Translate

Wednesday, February 24, 2021

# Dawwee Boora/ # ደዌ

የደዌ ቦራ ዘመቻና የአቶ መለስ ጉብኝት1984 ።
.
የዛኔ በሽግገሩ ወቅት (የደርግን ስርአት በትብብር በጣሉ ማግስት) በኦቦ ሌንጮ ለታ ይመራ የነበረው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) አንደ አንድ የነፃነት ታጋይ ድርጅት ለዘመናት የደከመለትን አላማ ለማስፈፀም ታግይለታለሁ በሚላቸው ጉዳዪች ላይ በሰአቱ ተደራድሯል ። ይብዛም ይነስም /አሻጥር ቢኖርበትም/ የተወሰኑ የስልጣን ወንበሮችን አልተነፈገም ነበር ፣ (የተወሰነ የሚኒስተር ሹመት ተሰጠው) ። ወዲያው አባላቶቼ አልያም ደጋፊዎቼ ይኖራሉ ብሎ ባሰበበት ያገሪቱ ክልልሎች ቢሮዎቹን ከፈተ ። ከነዛ መካከል ወሎ ከሚሴ ቢሮ ከተከፈተባቸው ከተሞች መካከል አንዷ ነበረች ። 

ለዘመናት ሲንከባለል የመጣው እጅግ አስቸጋሪ የማንነት ፈተና መፍትሄ ሊያገኝ ነው በሚል ህዝቡ  ተስፍን ሰነቀ። ምን ዋጋ አለው ሳይውል ሳያድር ደስታውን ገና አጣጥሞ ሳይጨርስ ማእበሉ ተማታ ፣ ኦነግ ከመድረኩ በዘዴ ተባሮ አገር ለቆ እንዲወጣ ተደረገ ።

 የህዝቡ ተስፍና ደስታ በቅፅበት እንደ ጉም በነነ ። በየቦታው የተከፈቱ ቢሮዎቹም በቀንም በማታ መፍረስ ጀመሩ፣ በሰአቱ የነበሩን የኦነግ ተሿሚዎች የመኖሪያ ቤት ሳይቀር በግፍ ፈራረሱ። የተሰቀሉ የኦነግ ባንዲራዎች እየወረዱ በእሳት ጋዩ፣ አይደለም ኦነግ መሆን ኦሮሞነት ማሸማቂያ (መጠቂያ) መሳሪያ ሆነ ፣ ይህ እጣ ከደረሳቸው ከተሞች መካከል አሁንም አንዷ ይቺው ልዩ ዞናችን ነበረች ።

1984 እርግጥ ነው ለዘመናት ለማንነታቸው (ለህልውናቸው) ሲታገሉ የነበሩት ያከባቢያችን ሰዎች የስርአት ለውጡ ባመጣው አጋጣሚ በመጠቀም በተለይ "ደዌ"  ላይ በማንነታቸው  ለህልውናቸው ሲሉ መደራጀት ጀመሩ። 

ይህ ሁኔታ ያላማረው መንግስት ነገሮችን ባይነቁራኛ መከታተል ጀመረ፣ በተለይ ተገፍቶ ከአገር የተባረረው ኦነግ ያደራጃቸው ሃይሎች በቦታው (ደዌ) ሊኖሩ እንደሚችሉ በመገመት ያገሪቱን ዋና ዋና ጀግኖች ማሳደድ መከታተልና ማዋከብ ጀመረ ። የዛኔ ነው እንግዲህ ህዝቡ ጀግኖቹ ሲሳደዱ ዝም ብሎ መመልከት አልያም አሳልፎ መስጠት ያመጣበትን ጉዳት ወደሃላ ተመልሶ ታሪኩን ማሰብ የጀመረው ። 

ነገሩ እንዲህ ነው በንጉሱ ዘመን ( አፄ ሃይለስላሴ ዘመነ መንግስት) ኦሮሞ መሆን በሚታፈርበት በሚናቅበት ዘመን መሆኑ ነው ክብራችን ተዋርዶ በማንነታችን ምክንያት ከሰው በታች ሆነን ከምንኖር እየታገልን መሰዋት ይሻለናል ብለው ያመኑ  ፣ባህላቸውን ፣ታሪካቸውን ሀይማኖታቸውን እና ቋንቋቸውን ለማስከበር የሚታገሉ የወሎ ኦሮሞ ጀግኖችን እያሳደደ ቢገድልም ታጋዪቹ  ከመመናመን ይልቅ እየበዙና ከመድከም ይልቅ እየጠነከሩ መሆናቸውን የተረዳው የአፄው ስርአት በተለይ በደዌ ከሚሴ እና አከባቢዋ ያሉትን የጀግና አመራሮችን ለማጥመድ አንድ ዘዴ ዘየደ ።

 በሰአቱ በሁሉም ዘንድ የሚከበሩና ተሰሚነት በነበራቸው በታላቁን የዱለቲ ሼክ ላይ ተፅኖ አሳደረ። 

ይቅር ( አውፍ) እንባባል በማለት አግባባ ምንም እንደማያደርጋቸውም ለሼኮቹ ቃል ገባላቸው ። የእርቅ ዝግጅት (መውሊድ) ደዌ "ገበያ አርፍቤ" ላይ በስፍት ተዘጋጀ ፣ ሾሆቹም በተገባላቸው ቃል መሰረት ጀግኖች ከጫካ ወጥተው ወደ እርቁ ቦታ እንዲመጡ አዘዙ በዛ መሰረት ስመጥር የነበሩ 40 የወሎ ኦሮሞ ጀግኖችና መሪዎች የሾሆቹን ጥሪ አክብረው ትጥቃቸውን እየፈቱ በተዘጋጀው የመውሊድ ስነስርአት ላይ ከተሙ ።

 በውሸት ምሎና ተገዝቶ ከዚህ ቦሃላ እኛም እናንተን አናሳድድም እናንተም እኛን ስሙ የኦሮሞ ታጋዮችም ከጫካ እንዲወጡ አድርጉልን እና ወደ ሰላማዊ ህይወታቸው ይመለሱ ። 

የሆነው ግን ሌላ ነበር ኦሮሞን ማጥፍት ኢስላምን ማጥፍት ነው የሚል አቋም ያለው የአፄው ጦር አድፍጦ እየተጠባበቀ ነበርና አከባቢውን  ከበበ ሁሉም ጀግኖች በሚያሳዝን ሁኔታ ተማረኩ ።

በሰአቱ ከተሰቀሉ የጀግኖች መሪ መካከል ታዋቂው የነፃነት ታጋይ 
" ሃሰን አሜ ዘራፍ " ይገኝበታል ፣ ሃሰን በሃሙስ ቀን በገያ መሃል የድሮ ፖሊስ ጣቢያ የአሁኑ ጫት ተራ በነበረው ትልቅ ዋርካ ዛፍ ላይ ነበር የተሰቀለው ። ይህ አሳዛኝ እና አስቆጪ አጋጣሚ በአከባቢው ህዝብ ላይ የማይሽር ጠባሳ ትቶ አለፈ እስካሁን ድረስም በእልህ መንፈስ ለሌሎችም አርአያ ይሆን ዘንድ በግጥም በዘፈንም እተሞገሱና እየተወደሱ ዘልቀዋል ።

 ለህዝብ መቀጣጫ ይሆኑ ዘንድም በከሚሴ ገበያ በባቲ ፣ ሰንበቴ፣  እና በሌሎች ህዝብ በሚሰበሰብበት ስፍራዎች ላይ በግፍ እያንጠለጠለ ገደላቸው ። 

 ከዛ አሳዛኝ ታሪክ ብዙ የተማረው ያከባቢው ማህበረሰብ ያስህተት እንዳይደገም በሚል  ጀግኖቹን የሚነካበትን ማንኛውንም አካል ለመፍለም ቆርጦ ነበር የተነሳው ። ወደታሪኩ ልመለስ ። መንግስት ደዌ ላይ አሉ የሚባሉትን ሃይሎች ለማጥናትና ለመደምሰስ እንዲረዳው ሶስት ሰላዪችን ላከ በሰአቱ የነበረው የደዌ አስተዳደር  የፀጉረ ልውጦችን ምንነትና ፍላጎት እስኪያጣራ ድረስ አሰራቸው

መንግስት ይህን ሁኔታ ሲሰማ  ከአሰራቸው ያከባቢው አስተዳደር ጋር ሳይወያይና ሳይደራደር ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የታሰሩትን ለማስፈታት እና የኦሮሞ ጀግኖችን ለማደን በሁለት የኦራል መኪና የተጫኑ ወታደሮችን በሰአቱ የባዶ 8 አዛዥ በነበረው ባለ አንድ እጁ ታጋይ "ዋለልኝ" መሪነት በሌሊት "ደዌ ቦራ" ላይ ዘመቱ ።

በሰአቱ የጀግኖቹ መሪ የነበረውን "መሃመድ በሺር ሃመዱ 
/ቀሎ/ቡሮኮ" እና ሌሎች ሁለት ጀግኞችን ሱብሂን ሶላት ሰግደው አረፍ ባሉበት ቦታ አድፍጠው ከበቧቸው ፣ ጀግኞቹ ውጊያውን ጀመሩ የቻሉትን ገድለው ሶስቱም ተሰው ።

 የደዌ ኦሮሞ እና በአፍር መካከል በድንበር አከባቢ በግጦሽ ምክንያት በተለያዩ ጊዜ ግጭት ይነሳ ስለነበር ኦሮሞዎቹ የራሳቸው የሆነ የጦርነት ህግ አላቸው አንደኛ አገር በጠላት ሲወረር ልዩ የሆነ የሚያሰሙት ድምፅ አለ ሁለተኛ, ያንን ድምፅ ሰምተው የሚዘምቱ ሰዎች ምናልባች በግል የሚፈላለጉ ፀበኞች (ባለጋራ) እንኳ ቢሆኑም በዛ ሰአት አይነካኩም በጋራ ሆነው ጠላትን ይፍለማሉ እንጂ ።

ይህ በሽማግሌዎች የተደነገገ ሁሉም የሚመራበት ያከባቢው ህግ ነው ።በዛ መሰረት ያንን ያድምፅ ተሰማ አንዱ ከሌላው እየተቀበለ ለሁሉም አስተጋባ ። 

ሁሉም ያለውን መሳሪያ በመታጠቅ በየተራራው ላይ መሸገ ። በሰአቱ የሰርግ ስነስርአት ላይ የነበሩ መንደሮች ፣ኩሳ ፣ ጋሽመሌ፣ ሞፍ እና ሌሎችም መንደሮች ስርጉን ትተው ለጥሪው ምላሽ በመስጠት ወሳኝ ቦታዎችን ያዙ ። በዛ መሰረት ከ"ቦራ" ግዳጃቸውን ጨርሰው ሲመለሱ የነበሩትን ወታደሮች ቀርማጫ "ዲቢኛ" የሚባል ቦታ ላይ ቀድሞ በመጠበቅ ጦርነቱን በይፍ ጀመሩት። ዲቢኛ ከአባቴ የትውልድ መንደር ከሆነችው" መዲኔ" አጠገብ ያለች ስፍራ ነች መዲኔ ፣ ገንደ ኢሮ፣ ቂለዋ፣ የሚባሉ ኮረብታ ላይ የመሸጉት የደዌ ጀግኖች ወደታች እያለሙ መተኮስ ጀመሩ ። አሁን ጦርነቱ ተጧጡፍል ። 
.
ሽማግሌው አያቴ አልይ ሙሄ ( አሏህ ይዘንለት) መንደሩ "መዲኔ" ላይ  የተጀመረውን ጦርነት "ካርቤኑን" በመያዝ ተቀላቅላል ። የስጋ ዘመዴ መሃመድ አባ እና ሁሴን አደሞ እዛው "ገንደ ኢሮ" በትግል ላይ ሳሉ ተሰው ። ጦሃ ሰይድ ሃሰንም  "ዲደ በረኬ" ላይ አብራሂም ሙሃመድ እና ሌሎችም በጀግንነት እየተፍለሙ እያለ ከወታደሮቹ በተተኮሰ ጥይት ተመተው ወደቁ ። ከተሰውት መካከል ለአብነት * መሀመድ በሺር ሀመዱ -* አህመድ ጀማል * መህመድ አብዱ ቡሩኮ -*መሀመድ አሊ አጎቴ -ጋሽመሌ * ጨምሮ ሌሎች ለጊዜው ስማቸውን ያላስታወስኳቸው 16 ሰዎች ባንድ ቀን ተሰው ። 
.
በዚህ ግርግር መካከል ከአፍር ድንበር በኩል የተለመደው ቤት የማቃጠል ከብቶችን የመዝረፍ ዘመቻ መነሳቱ ታወቀ የህዝቡ ጦር ለሁለት ተከፈለ ከፊሉ ድንበር ላይ እየተቃጠለ ያለው ቤት ለማትረፍና ከብቶቹን ለማስመለስ ወደዛው አመራ የተቀረው የዲብኛውን መጨረሻ ለማየት ትግሉን ቀጠለ ።

ሌላ ተጨማሪ ወታደር  በቴሌግራም ተጠርቶ ዘመተ፣ የጥይት ድምፅ ከሁሉም አቅጣጫ አንቧረቀ እናቶች ሳይቀሩ ወጣት ላጆቻቸውንና  ባሎቻቸው ተከትለው ወጡ እልልታው ፍከራው ቀለጠ ።  የጀግኖችን ሃይል እና ታክቲክ መቋቋም ያልቻለው ጦር መሸሽ ጀመረ ። በደዌዎች ተኩሶ መሳት አልያም ደረት መምታት ነውር ነው አብዛኛው ወታደር ግንባሩን ተመቶ ነበር የወደቀው ።

በዚህ መሃከል የጦሩ መሪ የነበረው " አንድ እጃሙ ዋለልኝ" በ ኒቫ መኪናው ለመሸሽ ሲሞክር ዲቢኛ ላይ ተይዞ ተገደለ ፣ መኪናውም ተቃጠለች ። በመጨረሻም "ሰላማ" የሚባል ቦታ ላይ ህዝቡ ድልን ተቀናጀ፣  ከፊሉ "ቀብር ዲብኛ " ውስጥ ሲገባ የተቀሩት ወደ መስጊድ ሸሹ ። ጋሽ መሌ፣ ሸመኒ፣ ካረከሎ ላይ በህይወት ተርፈውም ሆነ ቆስለው የተማረኩትን ወታደሮች ይዘው ወደ ሼሆቹ ጋር "ቢረንሰቆሬ" በመውሰድ በክብር አስረከቡ ። የሞቱትንም እጅግ በርካታ ወታደሮች ህዝቡ በዘመቻ ቀበሯቸው ። ልብ በሉ በአንድ ጊዜ በሁለት አቅጣጫ የተከፈተበትን ዘመቻ ህዝቡ በድል አጠናቋል ።

1985  በተለይ የታጋይ ዋለልኝ መገደል ጉዳዩን አገነነው፣ ወሬው  አዲስ አበባ ላይ መነጋገሪያ ሆነ አቶ መለስ ዜናዊን ጨምሮ የኢህአዴግ ከፍተኛ አመራሮች አከባቢውን ለማየትና ሁኔታውን ለማረጋጋት ወደ ደዌ ሃረዋ መሄድ እንደሚፈልጉ አሳወቁ ፣ በዛ መሰረት ለህዝቡ መንግስት እንደሚመጣ ቀድመው በማሳወቅ ከከሚሴ አቶ አሊ እብራሂም በሚባል ሰው መሪነት በኤሊኮኘተር ደዌ ቦራ ወረዱ ። በነገራችን ላይ ከከሚሴ ደዌ ቦራ 27 ኪ,ሜ ገደማ ይርቃል ።  

ያገር ሽማግሌዎች የሃይማኖት መሪዎችና ወጣቶችን በመሰብሰብ ስለተፈጠረው ችግር በስፍት ተወያዩ ። መንግስት  እንደሚያስበው  የተዋጋቸው ኦነግ ሳይሆን ያገሬው ህዝብ እንደሆነ አስረግጠው ተናገሩ ፣ በሰአቱ ህዝቡን ወክሎ ይናገር የነበሩት  የተከበሩት  አቶ "ቡሰይሪ" ነበሩ 

አቶ መለስ ዜናዊ በህዝቡ ጀግንነት እጅጉን ተደነቀ ሰፊ ውይይት ካደረጉም ቦሃላ መግባባት ላይ ተደረሰ ። በተለይ የፀቡ መነሻ የሆነው ጨለማን ተገን በማድረግ ምንም ያላጠፍ ህዝብ ላይ ወረራ በመፈፀም መግደል ተገቢ እንዳልነበር መንግስትም አምኖ ይቅርታ ጠየቀ ። ተወያዪችን  ምን እንደሚፈልጉ ጠየቃቸው እነሱም የማንነት ( ኦሮሙማ) ጉዳይ ላይ እንደማይደራደሩ አስረግጠው ተናገሩ ።

 በኦሮምነታችን ምክንያት ለዘመናት ዋጋ ከፍለናል ለወደፊትም ለመክፈል ዝግጁ ነን ፣ ከምንም ነገር በፊት ማንነታችን ታውቆ  ቋንቋችን ባህላችን ሊከበር ይገባል ፣ሌላው ነገር ከዛ ቦሃላ የሚቀጥል ነው የሚሆነው ። በማለት በአንድ ድምፅ አሳወቁ ፣ ብዙ ነገሮች ቃል ተገብቶላቸው ስብሰባው በሰላም ተጠናቀቀ ። አቶ መለስ ዜናዊም ወደመጡበት በክብር ተሸኙ። 


ሶለሊሃ ቀሊ ቆዳ ኢራ ባፈዱ 
ዋኤ ጆሌ ደዌ ኢሃዲግ ጋፈዱ 

የሆነው ሆኖ አገር ሲረጋጋ  አሉ የሚባሉ የነፃነት ታጋዪች ቀሰ በቀስ እንደየ ሁኔታው በሽፍታ ስም ላለፍት በርካታ  አመታት ተለቅመው በየአደባባዩ ላይ ተሰቀሉ ። 

 በኦነግና በአርማው በአሸባሪ ስም እጅግ ብዙ ያከባቢያችን ሰዎች ተገረፍ ፣ታሰሩ ተሰቃዩ ። ከፊሉ ጫናና ወከባው ሲያሰለቻቸው የሚወዱትን  ቤተሰቦቻቸውን ጥለው አገር ለቀው ተሰደዱ ፣የተቀረው ወድቆም ተነስቶም በሚችለው መብቱን ለማስከበር ሞከረ።

 (ለሞቱትም  አሏህ የጀነት ያድርጋቸው ) እንዲህ እንዲህ እያለ ያሁሉ ጉድ አልፎ ዛሬ ላይ ተደረሰ ።  ታሪክ ታሪክ ነው ዋጋ ተከፍሎበታል እና የምናውቀውን ከሞላ ጎደል አሳወቅናችሁ ። ደስ የሚለው ነገር  አንዱ አሳዳጅ ሌላው ተሳዳጅ የነበረበት ዘመን ግን አከተመ ። ጠቅላይ ሚኒስተር ዶ/ር  አብይ አህመድ እና ሁሉም የለውጥ አመራር በአዲስ መንፈስ በአዲስ አስተሳሰብ አገራችንን ኢትዮጵያን በጋራ ተረባርበን ለማሳደግ እና ሰላሟንም ለመጠበቅ ከያለህበት ክተት ብለው አወጁ ።እኛም ኖረን ይህንን ለማየት በቃን አይ መኖር ደጉ ።  

ነበገራችን ላይ ይህ ከታች የምትመለከቱት ፎቶ የታጋይ መሃመድ በሺር ነው ( አሏህ ይርሃመው) እጁን አነባብሮ የምትመለከቱት አቶ መለስ ዜናዊ  በሰአቱ ደዌ ቦራ ላይ ከገበሬው ጋር ሲወያይ የሚያሳይ ፎቶ ነው። 
/ የምንጩ ታሪክ ሙሀመድ አሊ/ የደዌ አባት
/ miky sultan/

ምንጭ አብዱ መሀመድ

No comments:

Post a Comment

mootittii saba'a Queen of sheba

"Mootittii Saba'a""Queen sheba" ----------------------------------------------------------------- ★Miky Sultan Bar...